Thursday, April 2, 2015

ሕጉን/ቃሉን/ ማሰብ


የዚህ ሕግ መጽሐፍ ከአፍህ አይለይ፥ ነገር ግን የተጻፈበትን ሁሉ ትጠብቅና ታደርግ ዘንድ በቀንም በሌሊትም አስበው የዚያን ጊዜም መንገድህ ይቀናልሃል ይከናወንልሃልም።  ኢያ ፩፣ ፰
ነገር ግን በእግዚአብሔር ሕግ ደስ ይለዋል፥ ሕጉንም በቀንና በሌሊት ያስባል። …. የሚሠራውም ሁሉ ይከናወንለታል።   መዝ ፩፣ ፩ - ፫
-      እግዚአብሔር ከሙሴ በኋላ ላስነሳው መሪ- ለኢያሱ- ከ፪ ሚሊየን በላይ ሕዝብ ለሚመራው፣ ከነዓንን ለማውረስ ላዘጋጀው ሰው ያስታጠቀው መሣሪያ - ቃሉን እንዲያስብ ነው።
o   የሚመራው ቀላል ሕዝብ አይደለም። በጉዞ የታከተው…
o   ከነዓን ምድሪቱ በአሕዛብ እጅ ስለሆነች ጦርነት አለበት።
፩. ሕጉ ምንድን ነው? –
የእግዚአብሔር ሕግ ፍጹም ነው ነፍስን ይመልሳል።  መዝ ፲፰/፲፱፣ ፯
ሕጉ፡- ፍጹም - እንከን የለሽ ነው። ሕጉ ለሰዎች የተሰጠ ነው። እግዚአብሔር ከሰዎች የሚፈልገውን የቅድስና መስፈርት ያሳያል። ወይም ለእግዚአብሔር ቅድስና ሰዎች መስጠት ያለባቸውን ምላሽ ያስቀምጣል።
ከእግዚአብሔር ጋር የሚኖረው /መኖር የሚፈልገው ሰው እንደ እግዚአብሔር ኃጢአት የሌለበት እንከን የለሽ መሆን አለበት።
ይህን ደግሞ ማድረግ ለሰው አልተቻለውም። በሕጉ መጽደቅ / በእግዚአብሔር ፊት የመቆም ብቃት ማግኘት/ አልተቻለም።
ይህም የሕግን ሥራ በመሥራት ሥጋ የለበሰ ሁሉ በእርሱ ፊት ስለማይጸድቅ ነው። ሮሜ ፫፣ ፳።
ሕጉን መሥራት/መፈጸም ባንችልም - ማሰብ ግን አለብን።
-       ሕጉን የምንፈጽመው በትዕዛዝ ግዳጅ - ሳይሆን በፍቅር መንፈስ ነው።
-       ፍቅር - የእኛ ጥረት ውጤት ሳይሆን እግዚአብሔር በእኛ ውስጥ የሚገልጸው የመንፈስ ቅዱስ ፍሬ ነው። --  ገላ ፭፣፳፪ - ፍቅር ከ፱ኙ የመጀመሪያው የመንፈስ ቅዱስ ፍሬ ነው። 
-       ሕጉን የምንፈጽመው በክርስቶስ ስንሆን እና በመንፈስ ቅዱስ የፍቅር ሰዎች ስንሆን ነው።
የሚያምኑ ሁሉ ይጸድቁ ዘንድ ክርስቶስ የሕግ ፍጻሜ ነውና።   ሮሜ ፲፣ ፬
ፍቅር ለባልንጀራው ክፉ አያደርግም፤ ስለዚህ ፍቅር የሕግ ፍጻሜ ነው።  ሮሜ ፲፫፣ ፲

Monday, March 16, 2015

እኔስ የመረጥሁት ጾም ይህ አይደለምን? (ክፍል ፪)

Chosen Fasting by God p 2 , READ IN PDF
ባለፈው ጽሑፋችን በትንቢተ ኢሳይያስ ምዕራፍ ፶፰ ስለጾም በሚናገረው ክፍል ጾማችን ምን መምሰል እንዳለበትና ምን መምሰል እንደሌለበት በማየት ከጥልና ከክርክር በመራቅ፡ በመልካም ምግባር መታጀብ እንዳለበት የሚገልጸውን የመጀመሪያውን ክፍል አይተናል። በዚህ ክፍል በጾማችን የምናገኘውን በረከት እናያለን።
ትንቢተ ኢሳይያስ ምዕራፍ ፶፰፡-
ቁ. ፰. የዚያን ጊዜ ብርሃንህ እንደ ንጋት ይበራል፥ ፈውስህም ፈጥኖ ይበቅላል፥ ጽድቅህም በፊትህ ይሄዳል፥ የእግዚአብሔርም ክብር በኋላህ ሆኖ ይጠብቅሃል
የዚያን ጊዜ የሚለው ቃል ከላይ ከነበረው ጉዳይ ጋር አያያዥ ነው። በክፍል ፩ ካየነው ሃሳብ የሚቀጥል ነው። ጾማችን ምን መምሰል እንዳለበት ተረድተን በተግባር የፈጸምነው እንደሆነ፡ ለሌሎች የነፍስ መዳን ንስሐን በማሰብ ከጠብና ክርክር በመራቅ፡ ፣ በፍቅር፡ በመልካም ምግባር፡ የተራበን በማብላት፡ የተጠማን በማጠጣት የታረዘን በማብላት…. የታጀበ ከሆነ የዚያን ጊዜ  የምናገኛቸውን በረከቶች ይዘረዝራል። ብርሃን፡ ፈውስ፡ ጽድቅ፡ ጥበቃ።
-  ብርሃን፡- ጨለማን የሚያስወግድ ክስተት ነው፡፡ በዓለም ለተፈጥሮው ጨለማ የፀሐይ ብርሃን ይወጣል። የሕይወት ጨለማ ለሆነው ጭንቀት፡ ተስፋ መቁረጥ ብርሃን ያስፈልጋል። ይህም ብርሃን በጌታ በደስታ በእረፍት ያለጭንቀት መኖር፡ነው። ጨለማ አያሳይም፡ ምንም የሕይወት ተስፋ በሌለበት፡ ምን እበላለሁ? ምን እጠጣለሁ?... ብለን ከምንጨነቅበት ሁኔታ ያስወጣናል፡ ሕይወታችን ይመራል። ምድራዊ በረከትን ያመለክታል።
- ፈውስ፡-  የሥጋም የነፍስም ሊሆን ይችላል። ለሥጋ በሽታ ሃኪም መድኃትን ቢያዝም ፈውስ ግን ከእግዚአብሔር ነው። ጾም ለበሽታ ፈውስ አንዱ መሣሪያ እንደሆነ ጌታ ተናግሮአል።«ይህ ዓይነት ግን ከጸሎትና ከጦም በቀር አይወጣም አላቸው።» ማቴ ፲፯፡፳፩።  የነፍስ በሽታ ኃጢአት ነው። በክርስቶስ በማመን የምናገኘውን የነፍሳችን ድኅነት (መዳን) ጠብቀን የምናቆየው በጾምና ጸሎት (በአምልኮ) እና በቅድስና በመኖር ነው። ስለዚህ ጾም የነፍሳችንን መዳን (ፈውስ) ለማቆየት አንዱ መሣሪያ ነው። ፈውስ ወይም መዳናችን እስከመጨረሻው ከጸና ለፍሬ ይደርሳል። እስከዚያ መብቀል (ማደግ) አለበት። ለዚህም ጾም ያስፈልጋል ማለት ነው። ፈውስህ ፈጥኖ ይበቅላል።.. ለፍሬም ይደርሳል። ማለት ነው። ለመንፈስ ቅዱስ ፍሬ። (ገላ ፭፡፳፪)
 

Friday, March 6, 2015

የኢየሱስ በዲያብሎስ መፈተን

« ከዚያ ወዲያ ኢየሱስ ከዲያብሎስ ይፈተን ዘንድ መንፈስ ወደ ምድረ በዳ ወሰደው፥
አርባ ቀንና አርባ ሌሊትም ከጦመ በኋላ ተራበ። ፈታኝም ቀርቦ…..» ማቴ ፬፣ ፩ - ፲፩
Ø ኢየሱስ ክርስቶስ በዮሐንስ መጥምቅ ከተጠመቀ በኋላ ምድራዊ አገልግሎቱን ከመጀመሩ በፊት በዲያብሎስ ተፈተነ፣- ከጾም ጋር ነበረ። - ለአገልግሎቱ የዝግጅት / የጽሞና ጊዜ ወሰደ።
Ø ክርስቶስ ወደ ምድረ በዳ በመንፈስ ቅዱስ ምሪት የተወሰደበት ዓላማ - ከዲያብሎስ ይፈተን ዘንድ - ነው።
-      ለምን ተፈተነ? - እግዚአብሔር ልጄ ስላለው ልጅነቱን ለማረጋገጥ፣ የዲያብሎስ አለመሆኑን - ወርቅ በእሳት እንደሚፈተን፡ - ማስመስከር ነበረበት።
-      ፈተናውን በድል ተወጥቶ ለእኛ እንድንማርበት፣ - ፍለጋውን እንድንከተል። ዲያብሎስን በፈተና ድል እንድናደርግ።
«የተጠራችሁለት ለዚህ ነውና፤ ክርስቶስ ደግሞ ፍለጋውን እንድትከተሉ ምሳሌ ትቶላችሁ ስለ እናንተ መከራን ተቀብሎአልና።»     ፩ ጴጥ ፪፣ ፳፩
Ø - ከዚያ ወዲያ-  ከምን? - ከምዕራፍ ፫፣ መጨረሻ- ተጠምቆ ከውሃ ሲወጣ - አብ በሰማይ ሆኖ ከመሰከረለት በኋላ- «… በእርሱ ደስ የሚለኝ የምውደው ልጄ ይህ ነው አለ።»
o   እግዚአብሔር ልጄ ብሎ መስክሮለት - የእግዚአብሔር ልጅ ሆኖ ዲያብሎስ እንዴት ቀረበው? - ድል እንዲያደርገው።
o   ጌታ በመንፈስ ቅዱስ መሪነት ስለተጓዘ - በቃሉ ኃይል ድል አድርጎታል።
o   እኛ በጸጋ የእግዚአብሔር ልጆች ነን። ይህ ማለት ሰይጣን አይቀርበንም ማለት አይደለም። በተለያየ መንገድ ሊጥለን ይቀርባል። ትልቁ ነገር ግን በመንፈስ ቅዱስ ምሪት እስከተጓዝን ድረስ - ምድረ በዳም እንግባ/ ምግብም አይኑር/ ዲያብሎስም ይምጣ - ቃሉን እስከታጠቅን ድረስ - ድል እናደርገዋለን። - የተረጋገጠ ጉዳይ ነው።
፩. ፈተናዎቹ - ፫ ናቸው -  /ስስት፣ ትዕቢት፣ ፍቅረ-ንዋይ - ይሉታል አባቶች/ - እንያቸው፡-
ü ፩. ድንጋዩን እንጀራ አድርግ - ቁ. ፪ - ፬ - ስስት- ፤ - በእግዚአብሔር መግቦት ላይ የቀረበ ፈተና
o   ጌታ ፵ ቀን ፵ ሌሊት ጾሞ ተርቦ ነበር። ዲያብሎስ እንደራበው አይቶ ነው የተናገረው፡- የእግዚአብሔር ልጅ ከሆንክ እነዚህ ድንጋዮች እንጀራ እንዲሆኑ በል- ሁለት ማሳመኛ
§  ፩. እርቦሃል - የሚበላ ነገር ያስፈልግሃል። በዚህ ምድረ በዳ ድንጋይ ብቻ ነው።
§  ፪. የእግዚአብሔር ልጅ ነህ - ድንጋዩን ወደ እንጀራ መለወጥ ትችላለህ።
እንደራበው እንዴት አወቀ? -- ያያል፣ ጌታ ምግብ አልበላም - በጾም ላይ ነውና።
የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑን እንዴት አወቀ? -ሰምቷል-- አብ በሰማይ ተናግሯልና።
         ስለዚህ ዲያብሎስ ስለእኛ የሚያውቀው ከድርጊታችንና ከቃላችን ብቻ ነው ማለት ነው። የልባችን አያውቅም፤ የልብን የሚያውቅ ባለቤቱ እና እግዚአብሔር ብቻ ነው።…

Friday, February 20, 2015

እኔስ የመረጥሁት ጾም ይህ አይደለምን? (ክፍል ፩)

God chosen fasting part 1, read in pdf
የያዝነው አርባ ጾም ዐቢይ (ታላቅ) ጾም እንደመሆኑ መጠን በመጽሐፍ ቅዱሳችን በምዕራፉ ሙሉ ስለጾም የሚናገረውን ትንቢተ ኢሳይያስ ም. ፶፰ ከሕይወታችን ጋር በማያያዝ መጽሐፍ ቅዱስ የሚያስተምረንን እናያለን።
ትንቢተ ኢሳይያስ ምዕራፍ ፶፰፡-
ቁ .፩  በኃይልህ ጩኽ፥ አትቈጥብ፥ ድምፅህን እንደ መለከት አንሣ፥ ለሕዝቤ መተላለፋቸውን ለያዕቆብ ቤትም ኃጢአታቸውን ንገር።
ኃጢአት ሰዎችን ከእግዚአብሔርን የሚለይ ሲሆን ንስሐ ወደ እግዚአብሔር እንዲመለሱ የሚያደርግ ተግባር ነው። ሰዎች ወደ እግዚአብሔር እንዲመለሱ ኃጢአታቸው ሊነገራቸው፡ እነርሱም ኃጢአታቸውን በመናገር ንስሐ ሊገቡ ይገባል። በዚህ ክፍል እግዚአብሔር ነቢዩ ኢሳይያስን ለአይሁድ ኃጢአታቸውን እንዲነግራቸው ያዘዋል። አይሁድ እግዚአብሔርን የሚያውቁና የሚያምኑ ሕዝቦች ቢሆኑም ጥፋታቸው ሊነገራቸው ይገባ ነበርና ነቢዩን ላከላቸው።
ዛሬ እግዚአብሔርን የሚያውቁና፡ በቤቱ ስለሚኖሩ ክርስቲያኖች ጥፋት ምን እያደረግን ነው? ጥፋታቸው ለራሳቸው ተነግሮአቸው ንስሐ እንዲገቡ ወይስ ለሌላው ተነግሮባቸው እንዲበረግጉ?  ወንድሞቻችን ምንም ዓይነት ጥፋት ያጥፉ ቁም ነገሩ ለምን አጠፉ? ሳይሆን እንዴት ይመለሱ? መሆን አለበት። አንድ ወንድም «ከጥፋቴ በፊት መጥፋቴ ያሳስባችሁ» ብሎአል። ብዙ ጊዜ ስለ ጥፋታቸው እንጂ ስለመጥፋታቸው አናስብም። እግዚአብሔር ግን ሁሉም በጥፋታቸው ተጸጽተው በንስሐ ይመለሱ ዘንድ ጥሪ እንድናደርግ በኃይልህ ጩኽ፥  ዝም እንዳንልም አትቈጥብ  ይለናል። በአንድምታውም ጩኽህ አስተምር፡ ማስተማሩን ቸል አትበል ይላል።
ከዚህ ሌላ ብዙዎቻችን በዓለም ያሉ ሰዎችን ኃጢአት በግልጽ መቃወም እንወዳለን። በቤቱ ላሉት ግን ጥፋታቸውን መናገር እንፈራለን። ሰባኪም ይሁን ተማሪ ከሊቅ እስከ ደቂቅ የሚታየው (ምናልባት ለራሳቸው የማይታያቸው) ጥፋታቸው ሊነገራቸው ይገባል። ለሕዝቤ  መተላለፋቸውን ንገር ይላል። ለሌላው ተናገር ሳይሆን ለራሳቸው ንገር።
ቁ.፪ . ነገር ግን ዕለት ዕለት ይሹኛል መንገዴንም ያውቁ ዘንድ ይወድዳሉ ጽድቅን እንዳደረጉ የአምላካቸውንም ፍርድ እንዳልተዉ ሕዝብ እውነተኛውን ፍርድ ይለምኑኛል፥ ወደ እግዚአብሔርም ለመቅረብ ይወድዳሉ።
አይሁድ የእግዚአብሔርን ሥርዓቱንና ሕጉን በመጠበቅ እግዚአብሔርን ማምለክ ይወዳሉ። እርሱን ለማስደሰት ሁሉንም ውጫዊ ሥርዓት ለመፈጸም አጥብቀው ይጠነቀቃሉ፡፡ በዚህም እግዚአብሔር ፍትህን እንዲሰጣቸው ይጠይቃሉ።  በአንድምታው በጎ ሥራ እንደሚሠራ ሰው ሁሉ ሕጌን ልታውቁ ትወዳላችሁ፡ ይላል፤ በጎ ሥራ የላቸውም ማለት ነው።
ዛሬም ብዙዎቻችን በምንፈጽማቸው ዕለታዊ የሃይማኖት ሥራዎች ወደ ቤተ ክርስቲያን በመመላለስ፡ እንደ ጸሎት፡ ጾም፡ ስግደት…ያሉ የአምልኮ ሥርዓቶችን በመፈጸም እግዚአብሔርን ለመቅረብና ደስ ለማሰኘት እንጥራለን። ይህ ጥሩ መነሻ ሊሆን ይችላል። ያለ በጎ ሥራ ይህ ትጋታችን ብቻውን በቂ እንዳልሆነ ይህ ክፍል ያስተምረናል።

Friday, December 12, 2014

እኔ ማን ነኝ?


እኔ….. ነኝ ብሎ በሥልጣን ቃል የተናገረ፡
በብሉይ ኪዳን፡ እግዚአብሔር ብቻ፡ ነው።….ሰባቱን ብናይ፡-
-      እኔ ለአንተ ጋሻህ ነኝ። ዘፍ ፲፭፣፩
-      እኔ ኤልሻዳይ ነኝ።. ዘፍ ፲፯፣፩
-      የአባቶችህ አምላክ እግዚአብሔር እኔ ነኝ። ዘፍ ፵፮፣፫
-      ያለና የሚኖር እኔ ነኝ። ዘጸ ፫፣፲፬
-      እኔ እግዚአብሔር ነኝ። ዘጸ ፮፣፫
-      ከግብጽ ምድር ከባርነት ቤት ያወጣሁህ እግዚአብሔር አምላክህ አኔ ነኝ። ዘጸ ፳፣፪
-      እኔ እግዚአብሔር አምላክህ ቀናተኛ አምላክ ነኝ። ዘጸ ፳፣፪
በአዲስ ኪዳን፡ ኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ፡ ነው።….ሰባቱን ብናይ፡-ለ
-      የሕይወት እንጀራ እኔ ነኝ። ዮሐ ፮፣፴፭
-      እኔ የዓለም ብርሃን ነኝ። ዮሐ ፰፣፲፪
-      እኔ የበጎች በር ነኝ። ዮሐ ፲፣፯
-      መልካም እረኛ እኔ ነኝ። ዮሐ ፲፣፲፩
-      ትንሣኤና ሕይወት እኔ ነኝ። ዮሐ ፲፩፣፳፭
-      እኔ መንገድና እውነት ሕይወትም ነኝ። ዮሐ ፲፬፣፮
-      እውነተኛ የወይን ግንድ እኔ ነኝ። ዮሐ ፲፭፣፩
እኔ…..እንዲህ… ነኝ ብሎ የተናገረና መናገር የሚችል አምላክ ብቻ ነው። ምክንያቱም፡-
፩. የማይለወጥ /የማይወሰን ስለሆነ፡
እንዲህ / እዚህ ነበርኩ። እንዲያ / እዚያ እሆናለሁ… አይልም። ቦታ ጊዜ ሁኔታ አይገድበውም።
እግዚአብሔር አይለወጥም፡ አይወሰንም።
ኢየሱስ ክርስቶስ ትናንትና ዛሬም እስከለዘላለምም ያው ነው።… ዕብ ፲፫፣፰

፪. ሁሉ በእጁ / በእርሱ ስለሆነ፡
እግዚአብሔር ሁሉን ፈጥሮአል፣ ሁሉን ይመግባል።
ኢየሱስ ክርስቶስ ሁሉ ከእርሱና በእርሱ ለእርሱም ነውና፤ ለእርሱ ለዘላለም ክብር ይሁን፤ አሜን። ሮሜ ፲፩፣፴፮።
፫. ከእርሱ በላይ ማረጋገጫ ስለሌለ፡
አንድ ነገር -- ነው / አይደለም-- የሚል ልዩነት ቢፈጠር በሦስተኛ / በበላይ አካል እንዲረጋገጥ ይደረጋል።
እግዚአብሔር ሌላ አስረጅ፣ ምስክር አያስፈልገውም። ከእርሱ በላይ የሚያረጋግጥ ስለሌለ።
፬. ነኝ ያለው የሆነውን ስለሆነ
ሁልጊዜ የነበረውን፣ የሆነውን፣ ወደፊትም የሚሆነውን ነኝ አለ።
ያልሆነውን፣ የማይሆነውን ነኝ አላለም፤ አይልምም።

Wednesday, December 3, 2014

የፈቃዱ ምሥጢር - ክፍል ፪

......ባለፈው ክፍል ኤፌ ፩፣ ፩ - ፲፬
.... በክርስቶስ ለማድረግ እንደ ወደደ እንደ አሳቡ፥ የፈቃዱን ምሥጢር አስታውቆናልና፤
በዘመን ፍጻሜ ይደረግ ዘንድ ያለው አሳቡም በሰማይና በምድር ያለውን ሁሉ በክርስቶስ ለመጠቅለል ነው።...
የሚለውን አሳብ ማየታችን ይታወሳል። ከዚህ ክፍል ምን እንማራለን? 
፩. ምሥጢረ-ሥላሴ፡-
Ø  መዳናችን የሥላሴ ሥራ ነው ። ሥላሴ - አብ ፣ ወልድ፣ መንፈስ ቅዱስ።
²  አብ - ዓለም ሳይፈጠር - አቀደ -- የአሳብ መነሻ - ልብ።
²  ወልድ - ዓለም ከተፈጠረ በኋላ - ሰው ሆኖ የአብን ዕቅድ ፈጸመ፣ ሞቶ አዳነን።
²  መንፈስ ቅዱስ - ዓለም ካለፈ በኋላ ለምንወርሳት መንግሥተ ሰማያት አሁን ማረጋገጫ /ማኅተም ሆነ።
፪. ምሥጢረ ሥጋዌ    
Ø  ቁ. ፫፡- የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክና አባት
²  አምላክ -ሲል- ክርስቶስ ፍጹም ሰው መሆኑን
²  አባት - ሲል- ክርስቶስ ፍጹም አምላክ መሆኑን - የአብ የባሕርይ ልጅ መሆኑን ያሳያል።
፫. ሁሉ በክርስቶስ እንደሆነና እንደሚሆን -  ሁሉ በእርሲ ሆነ ዮሐ ፩፣ ፫።
-      ከቁ .፩ - ፲፬ -- ኢየሱስ ክርስቶስ  ፲፬ ጊዜ ተጠቅሷል። -- በየቁጥሩ ማለት ይቻላል። ቃሎቹን ብናያቸው፡-
Ø  የኢየሱስ ክርስቶስ  ፩  ፫ 
Ø  በክርስቶስ ኢየሱስ  ፩ 
Ø  ከኢየሱስ ክርስቶስ  ፪  --- ምንጭን ያሳያል - የጸጋና የሰላም ምንጫችን እርሱ ነው።
Ø  በኢየሱስ ክርስቶስ  ፭
Ø  በውድ ልጁ  ፮  ፯
Ø  በክርስቶስ ፫  ፬  ፱  ፲  ፲፩  ፲፪  ፲፫
-      የኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያ - ባለቤትነቱን ያሳያል። እንደ ሐዋርያ ሆኖ የሚሠራ ማንኛውም አገልጋይ የኢየሱስ ክርስቶስ ነው። - የእገሌ ወይም የቤተ ክርስቲያን አይደለም።
Ø  ራሱን ያስተዋወቀበት ስም ነው።-  ክርስቶስ መታወቂያው ሆነ ፤ መታወቂያችን ሊሆን ይገባል።
-      ከኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ሰላም - ምንጭን ያሳያል። የተደረገልን የመዳን ጸጋ/ቸርነት እና ያገኘነው ሰላም ምንጩ ክርስቶስ ነው።

Friday, November 28, 2014

የፈቃዱ ምሥጢር - ክፍል ፩


በክርስቶስ ለማድረግ እንደ ወደደ እንደ አሳቡ፥ የፈቃዱን ምሥጢር አስታውቆናልና፤
በዘመን ፍጻሜ ይደረግ ዘንድ ያለው አሳቡም በሰማይና በምድር ያለውን ሁሉ በክርስቶስ ለመጠቅለል ነው።
ኤፌ ፩፣ ፱ - ፲  / ሙሉ ሃሳቡ ከቁ ፩ - ፲፬፤/
ፈቃዱ፡- ፍላጎቱ፣ አሳቡ፣ እቅዱ፣ ዓላማው፣ ውሳኔው ማለት ነው።
ምሥጢር፡- የማይነገር ስለሆነ ሳይሆን ተሰውሮ የኖረ በኋላ የተገለጠ ለማለት ነው።
ይህም የእግዚአብሔር የዘላለም ሃሳብ የሆነ መለኮታዊ ዕቅድ ነው።
-      ከቁ. ፫ - ፲፬፡- በግሪኩ አንድ ረጅም አረፍተ ነገር ነው፡፡ እኛም በአንድ አረፍተ ነገር ብናጠቃለው፡-
Ø  «እግዚአብሔር በክርስቶስ ለሆኑት ልጆቹ ስላደረገው መንፈሳዊ በረከት ክብር ምስጋና ይገባዋል።»  የሚል ይሆናል።
፩. ራሱን ማስተዋወቅ፡-  - የድሮ ደብዳቤዎች ሲጀምሩ ጸሐፊው ራሱን በመጥቀስ ነው።  
 ጳውሎስ ሐዋርያ የሆነው በእግዚአብሔር ፈቃድ ነው።
ከ፲፪ቱ ሐዋርያት ጋር አልተጠራም፤ በኋላ በክርስቶስ መገለጥ በልዩ አጠራር ተጠራ።
የመልዕክቱ አድራሻ፡- በኤፌሶን ላሉት፣ በክርስቶስ ላሉት - አሁንም ለእኛ፡፡ - ተዘዋዋሪ ደብዳቤ ነው ይሉታል።
፪. ሠላምታ፣-  ጸጋና ሠላም - የጳውሎስ የተለመደ ሰላምታ።
ጸጋ፡- እግዚአብሔር መዳናችንን የሰጠበት የራሱ ነጻ ስጦታ። ቸርነቱ አይለየን፤ ጤና ይስጥልን እንደማለት ነው፡
ሠላም፡- ከዳንን በኋላ በክርስቶስ የሚኖረን እረፍት -- ሠላም ለናንተ ይሁን።
፫. በረከት፡- በረከት፣ የባረከን፣ ይባረክ።  ይህ በረከት፡-
Ø  በክርስቶስ የተደረገ ነው፤ ምክንያቱም መርገም በሰይጣን መጥቶ ነበርና ፡በአዳምና በልጆቹ ዘፍ ፫ና ፬
Ø  ሰማያዊ ነው። - ምድራዊ አይደለም፡- ቀዳሚው ነገር ነው።
Ø  መንፈሳዊ ነው። - ሥጋዊ / ቁሳዊ አይደለም።
Ø  ዘላለማዊ ነው፡፡ - ጊዜያዊ አይደለም።
²  የሚቀድም፣ የማይቀር፣ ዘላለማዊ በረከት ነው - የተፈጠርንበት ዋና ዓላማ።